
የምርት ብክነት እንዳይኖር እየሠራ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ይታወቃል።
አቶ ነጋ ባንተይሁን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አርሶ አደር ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ መሬታቸውን በሰሊጥ፣ ጥጥ እና ማሽላ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርቱን ውጤታማ ለማድረግ ከእርሻ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በቅርበት በመከታተል አስፈላጊ ግብዓቶችንም መጠቀማቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በዚህ ዓመት በ700 ሄክታር መሬት ላይ ከዘሩት የሰሊጥ ሰብል 1 ሺህ ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውን አስታውቀዋል።
ምርቱ እንዳይባክን ወቅቱን ጠብቀው በበቂ የሰው ኀይል ማሰባሰባቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ ብክነት እንዳያጋጥማቸውም ምቹ በኾነ መጋዘን ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌሎች ያልደረሱ ሰብሎችም ወቅታቸውን ጠብቀው እንደሚሰበስቡም ተናግረዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑርሁሴን አብድልቃድር በዞኑ ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን 50 በመቶ የሚኾነው ምርት ተሰብስቧል ነው ያሉት፡፡
የደረሱ ሰብሎች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲሰበስቡ በተዋረድ ባለው የግብርና መዋቅር ምክረ ሀሳብ እየተሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስፈልገውን ያክል የሰው ኀይል ማግኘት ስጋት የነበረ ቢኾንም በቂ ሠራተኞች ወደ ዞኑ በመግባት ምርት የመሰብሰብ ሥራው ተከናውኗል ብለዋል፡፡



