
በክልሉ ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል
አማራ ክልል ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዘርፉ እገዛውን ማጠናከር እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የክልሉ ጤና ቢሮ “ጤና ለሁሉም” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ፎረም ዛሬ በባህርዳር ተካሂዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት በመድረኩ እንደገለፁት ቢሮው ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው።
ለዚህም ከፍተኛ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በጤና ተቋማት እንዲሟሉ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በ18 ሆስፒታል ብቻ በስፔሻሊስት ኃኪሞች ይሰጥ የነበረውን ህክምና አሁን ላይ ወደ 67 ጤና ተቋማት ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፥ በክልሉ ያሉ የስፔሻሊስት ኃኪሞች ቁጥርም 391 ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም ለረጅም ዓመታት ግንባታቸው ተቋርጦ የቆዩ የጤና ተቋማትን እስከ ቀጣዩ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙት ዘርፉም የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወኑ ያሉትን ሁሉን አቀፍ ተግባራት በመገንዘብ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ማገዝ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ዘበነ በበኩላቸው፥ የህዝብ ግንኙነት ዘርፉ ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ለዚህም የክልሉን የጤና ሁኔታ ለማሻሻልና የሚከሰቱ የጤና ወረርሽኝ ክስተቶችን ለመከላከልና ለህብረተሰቡ ፈጥኖ መረጃ በመስጠት የማሳወቅ፣የማስገንዘብ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቀጣይም ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ጤናማ አምራች ዜጋ እንዲሆን የክልሉን ህዝብ በማንቃት ላይ በማተኮር ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ፤ጤናማና የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር መረጃን በተቀናጀ አግባብ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በተዘጋጀው የህዝብ ግንኙነት ፎረም ላይ በክልል ቢሮዎች የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት አመራሮች ተሳትፈዋል።
ኢዜአ




All reactions:
5656
ጥሩ ነው