
“ቀዳሚው አየር መንገዳችን የሕዝባችን ጥያቄ ተቀብሎ ከነጻነት ማግስት የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዛሬ ታሪካዊ እለት ነው” አቶ አሸተ ደምለው
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ባለፉት አመታት ተቋርጦ የነበረው የሁመራ አየር መንገድ በዛሬው እለት በረራውን ጀምሯል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ባለፉት ሶስት አስር አመታት ነጻነቱን ተነፍጎ ቆይቷል ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው አየር መንገዱ የሕዝቡን ጥያቄ የመለሰ ጥልቅ ስራ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ መጀመሩ የዞኑን ኢንቨስትመንት በማነቃቃት በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ መስተጋብር ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ አንስተዋል።
ሕዝቡ አማራዊ ማንነቱ በህግ አግባብ ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለው ነጻነቱን ከተጎናጸፈበት እለት ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ከዞኑ ባለፈ ለአጎራባች ዞኞች የሚያገልግል መሆኑም ተናግረዋል።
ዞኑ የነጭ ወርቅ ምድር መገኛ ነው ያሉት አስተዳዳሪው በአካባቢው መጥተው ማልማት ለሚችሉ በር የሚከፍት ነውም ብለዋል።
ቀዳሚው አየር መንገዳችን የሕዝባችን ጥያቄ ተቀብሎ ከነጻነት ማግስት የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዛሬ ታሪካዊ እለት ነው ብለው ምላሹን ለሰጠን ለፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በሙሉ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።
አየር መንገዱ በመጀመሩ ደስተኞች መሆናቸውን ያነሱት ተሳፋሪዎች ከነጻነት ማግስት የነበረው አንዱ ጥያቄያችን ተፈቷል ብለዋል።
የዞኑ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመቀናጀት ያመጡት ውጤት ነው ብለው ለተደረገው ትልቅ ስራም ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።




