
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የቤተክርስቲያኗን የ75 ዓመታት ጥያቄ መለሰ።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የጸደቀውን ካርታ አስረክበዋል።
ከተመሠረተ 385 ዓመታት ያስቆጠረው እና አጼ ፋሲል እንዳሠሩት የሚነገርለት የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በዙሪያው የቦታ ይገባኛል ጥያቄ ሲያነሳ ኖሯል። ጥያቄው ለ75 ዓመታት በርካታ ውጣ ውረድ ማሳለፉን የቤተ ክርስቲያኑ አሥተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ተናግረዋል።
በየዘመኑ ባለፉ መንግሥታት የቤተ ክርስቲያኗን ጥያቄዎች እና ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ “የ75 ዓመታት ጥያቄ እና የቤተክርስቲያኗ የዘመናት ችግር ዛሬ ተፈትቷል” ብለዋል። የቤተ ክርሴቲያኗን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ያደረጉ የቀድሞ አገልጋዮች እና ይህ እድል የገጠማቸው የወቅቱ መሪዎችን አመስግነዋል።
ለቤተ ክርስቲያኗ የተዘጋጀውን ካርታ ከከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተቀብለው ለቤተ ክርስቲያኗ አሥተዳዳሪ ያስረከቡት የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱሱ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ችግሩ ዘመንን ያስቆጠረ እና ሲገፋ የመጣ እንደ ነበር አስታውሰዋል።
ካለፈው ችግር በመማር ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያኗን እንዲጠብቅ፣ እንዲያለማ እና ከመሪዎቹ ጋር በቅርበት እንዲነጋገርም አሳስበዋል። በመነጋገር፣ በመወያየት እና በመመካከር የማይፈታ ችግር የለም ያሉት ብፁዕነታቸው በሂደቱ የተሳተፋትን ሁሉ በቤተ ክርስቲያኗ ስም አመስግነዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ደኘው በከተማ አሥተዳደሩ ላለፋት ጊዜያት ከአምልኮ ቦታ ጋር የተያያዙ እና እስካሁንም ድረስ ያልተፈቱ ጥያቄዎች አሉ ብለዋል። ችግሮቹን እየለዩ እና እየተነጋገሩ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የመንበረ መንግሥት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ለ75 ዓመታት ሲንከባለል የቆየ እና አሁን ካሉ መሪዎች እጅ የደረሰ ችግር ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሩን ለመፍታት መቻል መታደል ነው ብለዋል።
የቤተ ክርስቲያኗ ጥያቄ በስምምነት እንዲጠናቀቅ መሪዎች በቅርበት ለመነጋገር የወሰዱት ቁርጠኝነት አበረታች መኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም መሰል ችግሮችን ለመፍታት እና ፍትሐዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
አሚኮ





hi