የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ገንዘብ ቢሮ እና ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በ5 ዞኖችና በ7 ወረዳዎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም የትግበራ ስምምነት ዛሬ በተመለከቱ ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ፈርመዋል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን፣ ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ለክልሉ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኑን ገልጸው፣ የክልሉን ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ ጉልህ ሚና ያለው ተቋም መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ አታላይ እንዳሉት፣ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የፕሮጀክት ስምምነቶችን ፈጽሟል። አሁንም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ አዲስ የፕሮጀክት ስምምነት መፈረሙ የአጋርነቱን ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በተሻለ ቅንጅትና ዕቅድ እንዲተገበሩ፣ ከመንግሥት ዕቅዶች ጋር ድግግሞሽ እንዳይፈጠር እና የክልሉ ሕዝብ ከፍተኛ ተጠቃሚነት እንዲያገኝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በተጨማሪም ሥራዎቹ እስከ ታችኛው አደረጃጀት ድረስ በተገቢ ክትትልና ድጋፍ እንዲፈጸሙ እና አፈጻጸማቸው በየጊዜው በጋራ እንደሚገመገም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ በጤና፣ በትምህርት፣ በሕፃናት ጥበቃና እንክብካቤ፣ በሥርዓተ ምግብ፣ በውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በሌሎች ልማታዊ ዘርፎች በ5 ዞኖችና በ7 ወረዳዎች የሚተገበሩ ሲሆን፣ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦላቸው ከ1 እስከ 5 ዓመት ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚተገበሩ ተገልጿል።
የፕሮጀክት ትግበራ ስምምነቱን የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን እና የወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ምዕራብና ምሥራቅ አማራ አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ አባተ በፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ፈርመዋል።