የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ለከተማዋ ንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው
የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ስራ መጀመር ለከተማዋ ንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የደብረ ማርቆስ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን ከቀናት በፊት መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ተመስገን ተድላ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ሥራ መጀመር በተለይም ኢንቨስትመንትን ከማጠናከር አንፃር ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ጊዜያቸውን በመቆጠብ እና በልማቱ ስኬታማ ከመሆን ባሻገር ለፈጣንና ቀልጣፋ የገበያ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ስራ መጀመር ለከተማዋ ንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በደብረ ማርቆስና አካባቢው ለኢንቨስትመንት ሰፊ እድሎች መኖራቸውን ያነሱት ኃላፊው ባለሃብቶች ይህንን እድል እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማዋ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ታመነች ታደለ፣ አቶ ነብዩ ብርሃኑ እና ወጣት ተጎዳን ፈጠነ፤ የረጅም ዓመታት ጥያቄያችን ተመልሶ ኤርፖርቱ ስራ በመጀመሩ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር የኢንቨስትመንትና ንግድን በማነቃቃት አዳዲስ የስራ እድል እንዲከፈት የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የኤርፖርቱ መገንባት ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥም ትልቅ አቅም መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የደብረ ማርቆስ ኤርፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ጥያቄ የ30 ዓመታት የአካባቢው ህብረተሰብ ጥያቄ የነበረ ሲሆን በለውጡ መንግሥት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምላሽ ያገኘ መሆኑ ይታወቃል።




