በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጄ.ማሲንጋ ጎንደር ከተማን ጎበኙ፤
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጄ.ማሲንጋ የንግድ ዲፕሎማሲን ለማበረታታት፣ የሰላምና መረጋጋት አስፈላጊነትን ለማጉላት እና የአሜሪካ የውጭ ድጋፍ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስገኝ ለማረጋገጥ ወደ ጎንደር ተጉዘው ከአካባቢው አመራሮች ጋር መክረዋል።
አምባሳደሩ ከክልልና ከአካባቢ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የንግድ ግንኙነትን ለማስፋፋት እና ግልጽ፣ ተገማችና ለቢዝነስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደርን የቱሪዝም አቅም ለማሳየት አምባሳደሩ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውንና በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር የተመዘገበውን ፋሲል ግቢ ጎብኝተዋል።
በተጨማሪም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው፣ በፕሬዝዳንት ሃሪ ኤስ. ትሩማን “ፖይንት ፎር” ፕሮግራም መሠረት የተጀመረውን የ70 ዓመታት የአሜሪካና የዩኒቨርሲቲው አጋርነት አክብረዋል።
አምባሳደሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሁሉን አቀፍ ሪፈራል ሆስፒታል ከሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመገናኘት፣ በአሜሪካ ድጋፍ የሚካሄዱ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) መከላከልና ሕክምና ፕሮግራሞች በአማራ ክልል ለተጠቃሚዎች ሕይወት አዳኝ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን በቦታው ተመልክተዋል።
በታኅሣሥ 2018 ዓ.ም. (ዲሴምበር 2025) በኢትዮጵያ መንግሥትና በአሜሪካ መካከል በተፈረመው 1.466 ቢሊዮን ዶላር የጤና ትብብር ስምምነት መሠረት የሚሰጠው ድጋፍ፣ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማጠናከር፣ በረጅም ጊዜ በውጭ ድጋፍ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና ከዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶች ለመጠበቅ ያግዛል ተብሏል።
አምባሳደሩ በአማራ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችን ከሚያስፈጽሙ ተቋማት ጋር በመገናኘት፣ የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም በሚያጠናክር መልኩ የክልሉን ጽናት የሚያበረታታ፣ ፈጣን፣ ተጠያቂነት ያለውና በውጤት ላይ ያተኮረ የሰብአዊ ምላሽ አቀራረብ ለማስቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
መረጃው የጎንደር ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው



