ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ለሌላቸው የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች የመስሪያ ቦታ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ
የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር በቤት ኪራይ እና በኑሮ ውድነት ጫና የተነሳ እየተሰቃዩ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደተናገሩት፤ ውጤታማ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የሚቸገሩ የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች የተካተቱበት በራስ አገዝ የመኖሪያ ቤት ማህበር 500 የሚደርሱ ማህበራትን በማደራጀት ቦታ ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በማሳለጥ ነዋሪዎችን በራስ አገዝ የመኖሪያ የቤት ማህበር በማደራጀት የቤት እጦት ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል አሰራር በመፍጠር ወደ ስራ የተገባ መሆኑንም አክለዋል።
እንደ ከተማ አስተዳደር በተያዘው እቅድ በ3 ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን በ1ኛው ምዕራፍ የመንግስት ሰራተኞች በ2ኛ ምዕራፍ በዚህ ከተማ እንዲያገኙ የተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ከመንግስት ሰራተኛው ጋር ጎን ለጎን አብረው እንደሚስተናገዱ እና በ3ኛ ምዕራፍ ልዩ ልዩ ነዋሪዎች የሚስተናገዱ ይሆናል።
ይህም በዲጅታል መታወቂያና መሰል መረጃዎችን እንዲሁም ዘመናዊ የማጥሪያ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ማግኘት ያለባቸው እንዲያገኙ በጥንቃቄ ይሰራል ብለዋል።
ተግባሩ በከተማ አስተዳደሩ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽ/ቤት አስተባባሪነት የሚከናወን ሲሆን የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟላ ማነኛውም ሰራተኛ እና ጡረተኛ የቦታ ባለቤት እንደሚሆን ነው ከንቲባው የተናገሩት።
መረጃው የባህርዳር ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ኮሙኒኬሽን የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
Facebook: http://facebook.com/AmharaCommunications
Telegram ፡ https://t.me/amharacommunications
Twitter: https://twitter.com/Amhara_GCAO
You Tube: https://www.youtube.com/@amharacommunication
Website: https://www.amharacomm.gov.et
Tiktok
