
የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት የጎብኝዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በመጠበቅ እና በማልማት የጎብኝዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘምም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የባሕር ዳር እና አካባቢዋ አስጎብኝ ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ ማስተዋል ዘለቀ በተለይ ወደ ሰሜኑ ኢትዮጵያ ያለውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ፣ ታሪክ እና ባሕል ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱሪስቶች ባሕር ዳር እንደ አንድ መዳረሻ ኾና ታገለግላለች ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር የጣና ገዳማት፣ የጭስ ዓባይ ፏፏቴ፣ የቤዛዊት ተራራ እና የዓሳ ገበያ በዋናነት በቱሪስቶች የሚታዩ ወይም የሚጎበኙ መዳረሻዎች ናቸው፡፡
ኾኖም ከከተማዋ በ31 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የጭስ ዓባይ ፏፏቴ ለቱሪስቶች ለማስጎብኘት የመንገዱ ወጣ ገባነት አስቸጋሪ መኾኑን ነው የተናገሩ፡፡
መንገዱ በተለይም ክረምት አስቸጋሪ ነው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ በአጠረ ጊዜ ደርሶ መመለስ የሚቻለውን የጉብኝት ሥርዓት በመንገዱ አለመመቸት ምክንያት ከግማሽ ቀን በላይ እንደሚፈጅ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የባሕር ዳር ቱሪዝም መምሪያም ኾነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ በመኾን የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያ አትርሳው ዓለም በከተማዋ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጉብኝት እና ለከተማ ነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለሀገር ውስጥም ኾነ ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል። ለአብነትም በደቅ ደሴት የቅድስት አርሴማ ወደብ እና የመንገድ ግንባታ ሥራ፣ የዘጌ ባሕረ ገብ የቱሪዝም መዳረሻ የእግረኛ መንገድ በመሥራት ለጎብኝዎች ምቹ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የእንጦስ ገዳምንም ከአደጋ ለመከላከል የእድሳት ሥራ መሠራቱን እና በርካታ ጀልባዎች ሊያስጠጋ የሚችል ወደብ እየተገነባ መኾኑንም ነው የተናገሩ፡፡
የተጠናቀቀው የዓባይ ድልድይም ለቱሪዝም መዳረሻነት ከሚያገለግሉ መሠረተ ልማቶች አንዱ ነው ብለዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ገዳማት ያሉ ቅርሶችን ከተለያዩ ችግሮች ለመከላከል እና ለዕይታ ምቹ ለማድረግ በርካታ ሙዚየሞች ተሠርተዋልም ነው ያሉ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ውስጥም በርካታ የአስፓልት፣ የጌጠኛ ድንጋይ እና ሌሎች የመንገድ መሠረተ ልማቶች እየተሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ከባሕር ዳር ጭስ ዓባይ የአስፓልት መንገድ ውል ተይዞ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ባለሙያው የአስፓልት ማንጠፍ ሥራ እንደተጀመረም አስገንዝበዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከጭስ ዓባይ ከተማ የቱሪስት መርጃ ማዕከል እስከ ጀልባ መያዣው ድረስ ተጨማሪ ለእግር ጉዞ የሚመች አለያም ተሽከርካሪ የሚያስገባ መንገድ ለመሥራት በውል የተካተተ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ አሁን ባለው የጸጥታ ችግር በተያዘው የጊዜ ገደብ እና በሚፈለገው ልክ ሥራውን ማፋጠን እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት፡፡
ይህንን ለማሳለጥ እና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እንደሚደረግም ነው የገለጹት፡፡
ከተማዋን ለቱሪዝም እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ከምትታዎቅባቸው ትላልቅ መዳረሻዎች መካከል የአማራ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎች ዋናዎቹ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በላሊበላ እና በስሜን ተራራዎች እና በአካባቢው የሚገኙት ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ከተሞች በዙሪያቸው በያዟቸው ቀላል የማይባሉ የመስህብ ሃብቶች ምክንያት የበርካታ የቱሪስት ዐይን ማረፊያ ናቸው።
ወደ አካባቢዎቹ የሚመጡ እንግዶች የመስህብ ሃብቶችን ይጎበኛሉ፣ እግረመንገዳቸውንም በየከተሞች በሚገኙ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም አገልግሎት ያገኛሉ ብለዋል፡፡
የቱሪስት ቆይታን ለማራዘምም ክልሉ እያለማ ባለው የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኾኑ ሆቴሎች እየተገነቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ በዚህም ክልሉ በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ስለመኾኑ ጠቡመዋልደ
አብዛኞቹ ከተሞች ከተጨናነቀ የመንገድ እና የመተላለፊያ ሥርዓቶች ወጥተው ሳቢ እና ማራኪ በኾነ ሁኔታ መንገዶች እየተሠሩላቸው እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የሚሠሩ የኮሪደር ልማቶችን ጠቅሰዋል።
ይህም ኾኖ ግን አሁንም በክልሉ ባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች መሠረታዊ የኾነ የመሠረተ ልማት ችግር ይታያል ነው ያሉ፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታትም ለቱሪስት መዳረሻዎች ጥርጊያ መንገዶችን በመሥራት ከዋና መንገዶች ጋር የማገናኘት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም አብዛኛው በክልሉ ያሉ የመስህብ ሃብቶች በተሽከርካሪ ተደራሽ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ ተሠርቷልም ብለዋል፡፡
የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥትንም መስፈርቱን ያሟላ ዓለም አቀፍ መዳረሻ ከማድረግ አንጻር አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት እና ግቢውን ሳቢ እና ማራኪ የማድረግ ሥራ እንደተሠራም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር የክልሉን የቱሪዝም አቅም ከማሳደግ አንጻር መልካም የሚባል ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ አሁንም ከዚህ በላይ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህንን ማድረግ ከተቻለ በየዓመቱ ክልሉን የሚጎበኘውን የቱሪስት ቁጥር በማሳደግ የሚገኘውን ገቢም ከፍ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉ።
በቱሪዝም ያለውን የኢንቨስትመንት ፍላጎትም ከፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ኮሙኒኬሽን ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጫኑ።
Facebook: http://facebook.com/AmharaCommunications
Telegram ፡ https://t.me/amharacommunications
Twitter: https://twitter.com/Amhara_GCAO
You Tube: https://www.youtube.com/@amharacommunication
Ticktock: https://www.tiktok.com/@amharacommunication…
Website: https://www.amharacomm.gov.et
