የአማራ ክልል የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ቢሮ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
የእንሰሳት ሃብት ልማት ስራዎች በምግብ ዋስትናችን እንድናረጋግጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተወካይ ከንቲባ አቶ ነፃነት መንግስቴ ገልፀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት ስራዎችንና ሌሎች የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ለሰጧቸው ገንቢ አስተያየቶች ትልቅ ክብር አለን ብለዋል።
የአማራ ክልል እንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ ይስማው ደግሞ የግምገማ መድረኩ ዓላማ ቢሮው በሩብ ዓመቱን የእቅድ አፈፃፀምን በመገምገም በሁለተኛው ሩብ ዓመት በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያስችላል ብለዋል።
በቀጣይ ቢሮው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ከሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አደረጃጀቶችና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
በዕለቱ የቢሮው የእቅድ ዝግጅት ባለሙያ አቶ ተመስገን ሽፈራው የቢሮውን የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፓርት አቅርበዋል።
የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ከግብርና ዘርፍ 47 በመቶ ይሸፍናል ያሉት ባለሙያው በውጭ ምንዛሬ ደግሞ 19 በመቶ የሚሸፍን መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ፣ የእንሰሳት ምጣኔን የተመለከተ ጥናት ማካሄድ፣ ለ17 ተጠሪ ተቋማት የደረጃ ማሻሻል ለመስራት የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ፣የእንሰሳትን መኖ ግብዓት መሟላት እንዲሁም የዘርፉን የ5ዓመት ስትራቴጅክ እቅድና የ25 ፍኖተ ካርታ ትግበራ የቢሮው ስትራቴጅክ ጉዳዮች መሆናቸው አመላክተዋል።
የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም አበረታች ነበር ያሉት ባለሙያው የወተትን ምርታማነት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት 730ሺ 194 ሊትር ወተት ለማምረት ታቅዶ 570ሺ 512 ሊትር ወተት በማምረት የእቅዱን 78 በመቶ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
በሩብ ዓመቱ 3 ሚሊየን 509ሺ 626 የቁም ከብቶችን ለገቢያ ለማቅረብ ታቅዶ 4ሚሊየን በላይ የቁም ከብቶችን ለገቢያ በማቅረብ የእቅዱን መቶ ፐርሰንት ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
በእንቁላል ምርት ደግሞ 240 ሚሊየን እንቁላል ለማምረት ታቅዶ 345 ሚሊየን እንቁላል ማምረት መቻሉን ገልፀዋል ።
በማር ምርት ደግሞ 333 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ 2ሺ661 ቶን ማር ማምረት መቻሉን የተናገሩት ባለሙያው 6ሺ437 ቶን ዓሳ ለማምረት ታቅዶ 7ሺ 384 ቶን ማምረት ተችሏል።
በእቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩ የምዕራብ አማራ ዞኖችና ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።



