

“ማንነታችንን ለማጽናት የማንከፍለው መስዋዕትነት የለም” አቶ አሸተ ደምለው
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የጠገዴ ወረዳ የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ አጠቃላይ የ6 ወራት ጠንካራ እና ደካማ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተደርጓል።
ሠላም እና ደኅንነት፣ ጤና እና ልማት የመድረኩ ዋና ዋና አጀንዳዎች ነበሩ።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በማንነቱ የማይደራደር ነው ያሉት አቶ አሸተ የማንነቱ ጉዳይ የእውነት፣ የፍትሕ እና የርትዕ ጥያቄ ነው ብለዋል።
ሠላሙን ስንጠብቅ፣ ልማቱንም ስናፋጥን የሕዝብ ጥያቄ ይመለሳል ነው ያሉት።
የተጀመሩ እና እየተሠሩ ያሉ የልማት ተግባራት በአመራሩ ሀሳብ አመንጭነት እና አሥተባባሪነት ፣ በሕዝብ ቀናኢ ደጋፊነት እና ተባባሪነት ነው ብለዋል። አሁን ሠላም ጠባቂዎች፣ ማንነትን አጽኝዎች እና ልማት ሠሪዎች ልንኾን ይገባል ነው ያሉት አቶ አሸተ።
“ማንነትን ለማጽናት የማይከፈል መስዋዕትነት እንደማይኖርም” ገልጸዋል።
የጠገዴ ወረዳ ሙሉ ሠላሙን በማረጋገጥ በልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዳደረገ የገለጹት ደግሞ የወረዳው አሥተዳዳሪ ጌታቸው ብርሃኔ ናቸው።
ከልማት አኳያ በወረዳው በዚህ ዓመት ሦስት ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የታቀደ ሲሆን ከእነዚህም አንዱን ፕሮጀክት በአልማ እና ሁለቱን ደግሞ በሕዝብ ተሳትፎ ለመሥራት እንቅስቃሴ ላይ መኾናቸውን አሥተዳዳሪው አብራርተዋል።
ተጀምረው የተቋረጡ ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች አሉ ያሉት አቶ ጌታቸው በተለይም የዓለም ገነት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልተጠናቀቀም ይህም ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል።
አሚኮ