

ኢትዮጵያዊ ኅብር በጎንደር ሰማይ ስር !
የጎንደሪያን ዘመን ተብሎ ዘመን በስሟ የተሰየመላት፣ ነገሥታት ዙፋናቸውን የገበሩላት፣ ቆነጃጅት ቁንጅናቸውን የናቁላት፣ ጀግኖች ክብራቸውን የተውላት፣ አረጋውያን መጦሪያቸውን፣ ሕጻናት ተስፋቸውን የገበሩላት ጎንደር በየዓመቱ አዲስ፤ ሁሌም ሙሽራ ናት።
የከተሞች እናት እየተባለች የምትጠራው ጎንደር እናት የሚለው መጠሪያዋ ዝም ብሎ የተቸራት ሳይኾን ታሪኳን፣ ቀዳሚነቷን እና ማንነቷን የሚገልጽ ነው። ከዛንዚባር ወዲህ ማዶ ከተማ ጥቀሱ ከተባለ ጎንደር ቀዳሚዋ ተጠቃሽ ቀደምት እና ጥንታዊ ናት።
ከ250 ዓመታት በላይ የሀገር መዲና ኾና ያገለገለችው ጎንደር የነገሥታቱ የእጅ ሥራ ውጤት ናት።
ጥንታዊ ነገሥታቱ ከተደጋጋሚ ጦርነት ትንሽ ፋታ አግኝተው ሲረጋጉ ዘመን ተሻጋሪ ከተሞችን መከተም የሚችሉ ጠቢባንም እንደ ነበሩ ጎንደር ብቁ ማሳያ ኾና ትታያለች።
ጎንደር ዛሬም ዘመን ሳይሽራት ዘመናዊነት ሳይበርዛት የትናንቱን ያስቀጠለች የጥንቱን ያነበረች ከተማ ኾና ዘልቃለች።
የ2017 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን ለማክበር ሽር ጉድ ላይ ያለችው ከተማ በዋዜማው ሁለት ታላላቅ መርሐ ግብሮቿን በስኬት እየቋጨች ነው።
15ኛው ጥምቀትን በጎንደር የባሕል ሳምንትና 16ኛው የአማራ ክልል የባሕልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲባል መርሐ ግብሮችን በድምቀት ያስተናገደችው ጎንደር ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ደርሳለች።
እንግዶቿን በፍቅር እና በክብር የተቀበለችው ጎንደር እንዳይረሷት አድርጋ እና አቀማጥላ አስተናግዳቸዋለች።
ጎንደርን ተዟዙረው ጎብኝተው እና ተመልክተው ያልጠገቧት እንግዶቿም በዜማቸው “ጎንደር ሰርክ አዲስ ናት” ብለውላታል።