

“በሀገር አቀፍ ደረጃ የባህል ንቅናቄ ከ4 ሚሊየን በላይ ህዝብ ተሳትፏል” ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የባህል ንቅናቄ እስከ አሁን ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ህዝብ ተሳትፏል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
“ድንቅ ምድር ድንቅ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የአማራ ክልል የባህልና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተጠናቋል።
በፌስቲቫሉ ላይ ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በህዝቦች መካካል ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ባህልና ኪነጥበብ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ባህልና ኪነጥበብ ለህዝቦች ትስስር መጠቀም እንዳለባት ገልጸው፤ ከህዳር 7 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የባህል ንቅናቄ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ህዝብ በቀጥታ መሳተፉን ተናግረዋል።
የዚህ ንቅናቄ አካል የሆነውና በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የባህልና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ በርካቶች መሳተፋቸው ተገልጿል።
የአፋርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የባህል ቡድኖችም የፌስቲቫሉ ድምቀት እንደነበሩ ተጠቁሟል።