ደም መለገስን ባህል በማድረግ በደም እጦት ምክናያት የሚሞቱ ወገኖችን መታደግ አለብን:: የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር)
ባ/ዳር፣ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አማራ ኮሙዩኒኬሽን) የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ድጋፍ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሰራተኞችና አመራሮች የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂደዋል።
በፕሮግራሙ የተገኙት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) ደም መለገስ የወላድ እናቶችን እና የተጎዶ ወገኖችን ህይወት ከመታደግ በላፈ የህሌና እርካታ እንዳለው ተናግረዋል።
ደም መለገስ የበርካታ ዜጎችን ህይወት እንዲቀጥል የሚያደርግ ሰብአዊ ተግባር ነው ያሉት መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) ዜጎች በደም እጦት ምክናያት ህይወታቸውን እንዳያጡ የሚያደርግ ነው፤ ሀገርንም መታደግ ነው ብለዋል።
በህይወት ዘመናችን ከምንሰራቸው የበጎ ፈቃድ ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው ደም መስጠት መሆኑን የገለጹት ኃላፋው ደም በመለገሳችን የምናጣው ነገር አለመኖሩን ተናግረው ይልቁንም ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ደም መለገስን ባህል በማድረግ በደም እጦት ምክናያት ዜጎች ህይወታቸው እንዳያልፍ ደም በመለገስ ልንታደጋቸው ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትብለጥ መንገሻ በበኩላቸው በየጤና ተቋሙ በደም እጦት ምክናያት በርካታ ዜጎች ህይወታቸው እንደሚያልፍ ተናግረው ደም መለገስ ከሠውነት ቅጥነትና ውፍረት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን ከተጓዳኝ በሽታዎች ከስኳር፣ ከደም ግፊትና ከሌሎች በሽታዎች ካሉባቸው ሰዎች በስተቀር፣ ወገንን ለመታደግ ሲባል በገንዘብ የማይተመነውን ደም ሁሉም መለገስ አለበት ብለዋል። የቢሮው ሰራተኞች በየሶስት ወሩ ደም እነደሚለግሱ ገልጸው እሳቸውም እንደ አንድ ዜጋ ለስምንተኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን አውስተዋል።
የቢሮው ሰራተኛ አቶ ቢልልኝ ልየው አካል ጉዳተኛ መሆኔ ደም ከመለገስ አላገደኝም፤ በዚህም ለሶስተኛ ጊዜ ደም ለግሻለሁ፤ ባደረኩት በጎ ተግባርም በጣም ደስተኛ ነኝ ብለዋል። በደም መለገስ ምክናያት የሚሞቱ የሚመስላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ የያዙ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉ ተናግረው ተጓዳኝ በሽታ ከሌለባቸው ሰዎች ውጭ ጤነኛ የሆነ ሰው ሁሉ ደም በመለገስ የወገኖቻችንን ህይወት መታደግ እንደሚገባ አቶ ቢልልኝ አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ ደም ለሁለተኛ ጊዜ እንደለገሱ የሚገልጹት የቢሮው ሰራተኛ አቶ ይልማ ዘውዴ እስካሁን ድረስ በነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ምክናያት ደም መለገስ አለመቻላቸው ቁጭት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
